በቀጣይ 15 አመታት የህጻናት የምግብ እጥረትን ለማስወገድ የሚያስችል ስምምነት በሰቆጣ ተፈረመ

 

(ነሃሴ 26፣ 2007)  በሚቀጥሉት 15 አመታት በህጻናት ላይ የሚከሰተውን የምግብ እጥረት ለማስወገድ የሚያስችል ስምምነት በሰቆጣ ዛሬ ተፈርሟል።ስምምነቱንም  ዘጠኙ ክልሎች እና ሁለቱ የከተማ አስተዳደሮች ናቸው ከጤና ጥበቃ ሚኒስቴር ጋር የተፈራረሙት ።

እስከ 2022 ዓመተ ምህረት በህጻናት ላይ የሚከሰተውን የምግብ አጥረት ከኢትዮጵያ ለማስወገድ ነው ስምምነቱ የተፈፀመው።በስምምነቱ ወቅት ንግግር ያደረጉት የጤና ጥበቃ ሚንስትሩ ዶክተር ከሰተብርሃን አድማሱ በ1977 ዓ.ም በኢትዮጵያ ተከስቶ በነበረው ድርቅ የወረዳው ህጻናት በከፍተኛ ሁኔታ ለምግብ እጥረት መጋለጣቸውን አስታውሰው፥ የዚህ አይነቱ የከፋ የምግብ እጥረት ባይከሰትም የህጻናት መቀንጨር በተለይም በዚህ አካባቢ እየተከሰተ በመሆኑ ስምምነቱ አስፈልጓል ብለዋል።

የመቀንጨር አደጋውን በቀጣይ ከሀገሪቱ ለማሰወገድ ቃል የሚገባበት እንዲሆን ስፍራው መመረጡንም ጠቅሰዋል።የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ገዱ አንዳርጋቸው በበኩላቸው፥ ስምምነቱ ለህፃናት የሚደረገው ሁለንተናዊ ድጋፍን ለማጠናከር ያግዛል ነው ያሉት።በስምምነት መርሃ ግብሩ ላይ የኢፌዴሪ ምክትል ጠቅላይ ሚኒሰትር አቶ ደመቀ መኮንንን ጨምሮ ሌሎች ከፍተኛ የመንግስት ባለሰልጣናት፣ የአካባቢው ነዋሪዎች ተወካዮችና ሌሎችም ባለድርሻ አካላት ተገኝተዋል።

(ኤፍ.ቢ.ሲ)

Tags: