በእርግዝና ወቅት የሚወሰዱ ምግቦች ለሚወለደው ልጅ የልብ ጤንነት ወሳኝ ነው ተባለ

 

እናቶች በእርግዝና ወቅት እና መውለጃቸው እየተቃረበ በመጣ ቁጥር የሚያደርጓቸው ነገሮች ለራሳቸውም ሆነ ለሚወለደው ልጅ ጤንነት የራሱ አስተዋጽኦ ይኖረዋል።በተለይም በእርግዝና ወራት የሚያደርጓቸው ነገሮች ለልጁ ጤንነት ወሳኝ መሆኑን፥ የተደረጉ ጥናቶች ያሳያሉ፤ የቅርብ ጊዜ ጥናት ደግሞ በዚህ ወቅት የሚወሰዱ የምግብ አይነቶች ለሚወለደው ልጅ የልብ ጤንነት ወሳኝ መሆኑን አንስቷል።

እንደተመራማሪዎቹ የተመረጡ እና የተሻሉ የምግብ አይነቶችን ከእርግዝና በፊትም ሆነ በእርግዝና ወራት አመጣጥኖ መውሰድ ልጅ ሲወለድ አብረውት ከሚመጡ የልብ እና ተያያዥ ችግሮች መከላከል ያስችላል።19 ሺህ ሴቶችን ያሳተፈው ይኼው ጥናት ሴቶች ከእርግዝና የመጀመሪያ ወራቶች ጀምረው የሚወስዷቸውን ምግቦች መሰረት አድርጎ የተገኙ ውጤቶችን አመላክቷል።

በዚህ ወቅትም ትኩስ አሳ፣ ፍራፍሬዎች፣ ለውዝ እና የአትክልት ዘሮች፤ ለእርጉዝ ሴቶች የሚመከሩ ምግቦች ናቸው።በጥናቱ ከተሳተፉት መካከል በባለሙያዎቹ የተዘረዘሩትን ምግቦች ከእርግዝና በፊትም ሆነ በእርግዝና ወቅት የሚወስዱ ሴቶች የሚወልዷቸው ልጆች ከማይወስዱት ይልቅ ጤነኛ የልብ ስርአት ያላቸው ሆነው ተገኝተዋል።

ተመራማሪዎቹም እነዚህ ምግቦች ለሴቶቹ ላቅ ያለ ጠቀሜታ እንዳላቸው በመጥቀስ አዘውትሮ መመገቡ መልካም መሆኑን በጥናታቸው አሳይተዋል።ከዚህ ባለፈም ፎሊክ አሲድ ያለበትን ቪታሚን ቢ9ን እና በቪታሚን ዲ የበለጸጉ ምግቦችን  መውሰድም ልጅ ሲወለድ ከሚያጋጥመው የአጥንት እና ተያያዥ ችግሮች መታደግ እንደሚያስችልም ነው የሚናገሩት።

ህጻናቱ አብረዋቸው ከሚፈጠሩ የተለያዩ የጤና እክሎችም በመከላከልም ንቁ እንዲሆኑ እንደሚያደርጋቸውም በጥናታቸው አሳይተዋል።ህጻናት ከውልደታቸው ጀምሮ አብሯቸው የሚመጣው የልብ ህመም ችግር በህጻናት ላይ የሚከሰትና ከ1 ሺህ ህጻናት መካከል 9ኙን የሚያጠቃ አስቸጋሪ የህጻናት በሽታ ነው። 

ምንጭ፥ ቢቢሲ፣ ኤፍ ቢ ሲ

Tags: