ማንኛውንም የጤና ምርመራ በሀገር ውስጥ ለማድረግ የሚያስችል ላቦራቶሪ ስራ ጀመረ

 

(ሀምሌ 30፣ 2007) የጤናው ዘርፍ የህብረተሰቡን ፍላጎት የሚያሟላ ለማድረግ የሚሰሩ ስራዎች ተጠናክረው ሊቀጥሉ እንደሚገባ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን አሳሰቡ።ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ የኢትዮጵያ የህብረተሰብ ጤና ኢንስትቲዩት ያስገነባውንና ማንኛውንም የጤና ምርመራ በሀገር ውስጥ ለማድረግ የሚያስችለውን ላቦራቶሪ በይፋ አስጀምረዋል።

ለስድስት ወራት ያህል አስፈላጊው ግብዓት ሲሟላለት የቆየው ላብራቶሪው ስራ መጀመሩ ታካሚው የህክምና መርመሪያ መሳሪያን በመፈለግ የሚፈጠርበትን መጉላላት እና ከአገር ውጪ ለማስመርመር የሚወጣውን ከፍተኛ ወጪም የሚያስቀር ነው።

መሰል ላቦራቶሪዎችን ከዚህ በላይ በማዘመን የተጠናከር ስራ ሊሰራ ይገባልም ብለዋል።የጤና ጥበቃ ሚኒስትሩ ዶክተር ከሰተ ብርሃን አድማሱ በበኩላቸው፥ አለም የደረሰበትን የጤና ቴክኖሎጂዎች በሀገር ውስጥ ለመፍጠር የሚያስችሉ ስራዎች እየተሰሩ መሆናቸውን ነው የተናገሩት።

መከላከልን መሰረት ያደረገው የአገሪቱ የጤና ፖሊሲ መሰል ዘመናዊ የህክምና አገልግሎት ተደራሽነት መስፋፋቱ  ከፍተኛ እገዛ እንደሚያደርግለትም ሚንስትሩ ገልፀዋል።አዲሱ የላቦራቶሪ መሳሪያ በአምስቱ የፌደራል ሆስፒታሎች አገልግሎት በመስጠት የሚጀምር ሲሆን፥ በቀጣይም በሌሎች ሆስፒታሎች ስራ ላይ ይውላል ነው የተባለው።

(ኤፍ.ቢ.ሲ)

Tags: