የኢትጵያ ሚድዋይፎች ማህበር ለምግብነት የሚውሉ የዛፍ ችግኝ በመትከል “የአረንጓዴ አሻራ” አካሄደ

ለምግብነት የሚውሉ ችግኞችን መትከል ጤናማ ትውልድን ለማፍራት ከማስቻሉም ባለፈ ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ እንደሚኖራቸው ተገልጿል፡፡  መርሃ ግብሩም “ከኮሮና ቫይረስ እራሳችንን እየጠበቅን የአረንጓዴ አሻራችንን እናሳርፋለን” በሚል መሪ ሃሳብ ተካሂዷል፡፡  ማህበሩ የአረንጓዴ አሻራውን ያሳረፈው “በአራብሳ ጤና ጣቢያ” ቅጥር ግቢ ነው፡፡ በእለቱም እንደ ማንጎ፣ ፓፓያ፣ ዘይቱን እና ሙዝ  ያሉ ለምግብነት የሚውሉ 200 ያህል የአትክልትና ፍራፍሬ ችግኞች ተተክለዋል፡፡ በማህበሩ አስተባባሪነት ከጤና ሚኒስቴር፣ ከአዲስ አበባ ጤና ቢሮ፣ ከማህበሩ አመራርና አባላት እንዲሁም ከአራብሳ ጤና ጣቢያ የተውጣጡ ባለሙያዎች ተሳትፈዋል፡፡

የኢትዮጵያ ሚድዋይፎች ማህበር ፕሬዚዳንት አቶ ዘነበ አካለ ከአረንጓዴ አሻራ በስተጀርባ ንፁህ አየር እና ጤናማ አካባቢ ለማግኘት ያስችላል ብለዋል፡፡ ማህበሩ እንደ ጤና ማህበር የተሻለ አካባቢን ለመፍጠር ከጤና ሚኒስቴር፣ ከክልል ጤና ቢሮዎች እና ሌሎች የሙያ ማህበራት ጋር በቀጣይም አብሮ እንደሚሰራ ተናግረዋል፡፡ የተተከሉት ችግኞች ለምግብነት የሚውሉ መሆናቸውን የጠቆሙት ፕሬዚዳንቱ፤ ”ማህበረሰቡ የተመጣጠነ ምግብ በማግኘት ጤናማ እንደሆን ያግዛል” ብለዋል፡፡

 

 

የኢትዮጵያ ሚድዋይፎች ማህበር ዋና ዳይሬክተር አቶ የሽጥላ ተስፋየ በበኩላቸው የፍራፍሬዎቹ መተከል ንጹህ አየር ለማግኘትና የአየር ንብረት መዛባትን ለመከላከል እንደሚያስችሉ ተናግረዋል፡፡ ማህበሩ በእናቶች እና ህጻናት ጤና ላይ እንደሚሰራ ያስታወሱት ዋና ዳይሬክተሩ፤ ”ለምግብነት የሚውሉ ችግኞችን መትከል ደግሞ ጤናማ ትውልድን ለማፍራት የማይተካ ሚና አላቸው” ብለዋል፡፡

“የአረንጓዴ አሻራ ማሳረፍ በአለም ላይ የሚከሰተውን የአየር ንብረት ለውጥ ለመከላከል ከፍተኛ አስተዋጽኦ ያደርጋል” ያሉት ደግሞ በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ጤና ቢሮ የእናቶችና ህጻናት ጤና አገልግሎት ዋና ዳይሩክተር ወይዘሮ ቤተልሔም ታዬ ናቸው፡፡ የጤና ባለሙያዎች በየስራ ቦታዎቻቸው የአረንጓዴ አሻራቸውን እያኖሩ ስለመሆናቸውም ጠቁመዋል፡፡ ከተሳተፉት የጤና ሙያተኞች አንዱ አቶ አብዮት ጌታ “እንደ ማንጎ፣ ፓፓያ፣ አቮካዶ፣ ብርቱካን እና ሌሎች ለምግብነት የሚውሉ እጽዋትን መትከል የሚያስደስት ተግባር ነው” ብለዋል፡፡

የአራብሳ ጤና ጣቢያ ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ሰመር ጌታሁን በበኩላቸው “በቅጥር ግቢው የተተከሉት ችግኞች እንደ ልጅ እንክብካቤ እንደማይለያቸው” ተናግረዋል፡፡ በአገሪቱ የተደራጁ የሙያ ማህበራትም እራሳቸውን ከኮሮና ቫይረስ በመጠበቅ የአረንጓዴ አሻራቸውን ማሳረፍ እንዳለባቸውም ጥሪ ቀርቧል፡፡

Tags: