የኢትዮጵያ ሚድዋይፎች ማኅበር 400 ሺህ ብር የሚያወጡ የሕክምና መገልገያ ቁሳቁሶችን በአማራ ክልል ለሚገኙ ስድስት ጤና ተቋማት ድጋፍ አደረገ

የኢትዮጵያ ሚድዋይፎች ማኅበር የኮሮና ቫይረስን ለመከላከል የሚያግዝ ግምታቸው 400 ሺህ ብር የሆኑ የሕክምና ቁሳቁሶችን ለአማራ ክልል ጤና ቢሮ ድጋፍ አደረገ። ማኅበሩ ድጋፉን ያደረገው 28ኛው ዓለም አቀፍ የሚድዋይፎች ቀን ምክንያት በማድረግ መሆኑን በርክክቡ ወቅት የማኅበሩ ፕሮግራም አስተባባሪ አቶ መላኩ ታምር ገልጸዋል። ከድጋፉ መካከል 330 ባለአንድ ሊትር ሳኒታይዘር፣ 551 የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ ጭምብሎች፣ 53 ለሕክምና ባለሙያዎች የሚያገለግሉ አልባሳት ይገኙበታል። ቁሳቁሶቹ በሽታውን በመከላከል ላይ የሚገኙ የጤና ባለሙያዎች ራሳቸውን ከቫይረሱ በመጠበቅ ሙያዊ አገልግሎት እንዲሰጡ የሚያግዛቸው መሆኑን አስረድተዋል።

“ማኅበሩ ድጋፍ ማድረጉ ሊያስመሰግነው ይገባል” ያሉት ደግሞ በክልሉ ጤና ቢሮ የጤና ማበልጸግና በሽታ መከላከል ዳይሬክተር አቶ መልሰው ጫንያለው ናቸው። ቁሳቁሶቹም ለባሕርዳር ፈለገ ሕይወትና የባሕርዳር ዩኒቨርሲቲ ጥበበ ግዮን ስፔሻላይዝድን ጨምሮ ለስድስት ሆስፒታሎች እንደሚሰራጩ አስታውቀዋል። የኢትዮጵያ ሚድዋይፎች ማኅበር የአማራ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ፕሬዚደንት አቶ መሳፍንት ዕውነቱ በበኩላቸው የኮሮና ቫይረስ እያደረሰ ያለውን ችግር በማቃለል የወገናቸውን ሕይወት ለመታደግ የማኅበሩ አባላት ሕይወታቸውን ሰጠው ሙያዊ ግዴታቸውን በመወጣት ላይ እንደሚገኙ ገልጸዋል።

“ሚድዋይፎች ከእናቶች ጎን ነን” በሚል መሪ ሀሳብ 28ኛው ዓለም አቀፍ የሚድዋይፎች ቀንም በክልል ደረጃ ዛሬ ታስቦ ውሏል። ማኅበሩ በሀገር አቀፍ ደረጃ አንድ ሚሊዮን 600ሺህ ብር ግምት ያላቸው የሕክምና ቁሳቁሶችን ድጋፍ ማድረጉም ተመልክቷል።

https://www.facebook.com/AmharaMassMediaAgencyAMMA/posts/1257369814438010

Tags: