የሚድዋይፍ እና ነርስ ባለሙያዎች በጤና እንክብካቤና ኮቪድ-19ኝን ለመከላከል የሚጫወቱት ሚና ከፍተኛ መሆኑ ተገለጸ፡፡

ሚድዋይፎች እና ነርሶች ለእናቶች ፤ ለህጻናት፣ ለልጆች፤ ለወጣቶች፤ እና ለአፍላ ወጣቶች አዛውንቶችን የጤና እንክብካቤ በማድረግ ሕይወታቸውን የሚያሳልፉ፣ ሕይወት አድን ክትባቶችን እና የጤና ምክሮችን የሚሰጡ፣ የሚንከባከቡ፣ ኮሮና ቫይረስ (ኮቪድ-19)ን ለመከላከል እና በአጠቃላይ የዕለት ተዕለት አስፈላጊ የጤና ፍላጎቶችን የሚያሟሉ ናቸው፡፡ ይህንን ጉልህ ሚና በመገንዘብ የዓለም ጤና ድርጅት የ2020 ዓመትን “የሚድዋይፍ እና የነርስ ዓመት” በማለት አውጆታል፡፡ በመሆኑም በአሉን የጤና ሚኒስቴር፤ የኢትዮጵያ ነርሶች ማህበር እና የኢትዮጵያ ሚድዋይፎች ማህበር ከተባበሩት መንግስታት የስነ ህዝብ ፈንድ ጋር በመሆን በብሔራዊ ደረጃ በጋራ ተከብሯል፡፡

ሴቶች 70 በመቶ የሚሆኑት የጤና ሠራተኛውን ይወክላሉ፤ ከእነዚህ ውስጥ ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ሚድዋይፎች እና ነርሶች ናቸው። ሚድዋይፎች እና ነርሶች በየቀኑ፣የጤና አገልግሎት በመስጠት ላይ ይገኛሉ፡፡ እነዚህ ባለሙያዎች በጤና እንክብካቤና ኮቪድ-19ኝን ለመከላከል በሚጫወቱት ሚና በእለቱ በጤና ሚኒስቴር እውቅና ተሰጥቶል፡፡

የጤና ባለሙያዎች ኮቪድ-19ኝን ለመከላከል ለሚያደርጉት ጥረት የኢትዮጵያ ሚድዋይፎች ማህበር በሽታውን ለመከላከል የሚረዱ 1 ነጥብ 6 ሚሊዮን ብር የሚገመቱ የሕክምና ቁሳቁስ በሁሉም ክልሎችና ከተማ መስተዳድሮች ለሚገኙ የህክምና ተቋማት ማሰራጨት መጀመሩን አስታውቋል፡፡

ሚድዋይፎች እና ነርሶች ግማሽ(50 በመቶ) የሚሆነው የዓለም የጤና ባለሙያዎችን ይይዛሉ፡፡ የተባበሩት መንግስታት ከፍተኛ ኮሚሽን የጤና ቅጥር እና የኢኮኖሚ እድገት ሪፖርት እንደሚያሳየው በጤና እና በማህበራዊ ዘርፎች ውስጥ የትምህርት እና የስራ ፈጠራ ኢንቨስትመንቶች ማሻሻል የጤና ውጤቶችን፣ የአለም አቀፍ የጤና ደህንነትን እና አጠቃላይ ኢኮኖሚያዊ እድገትን በሶስት እጥፍ ለመጨመር እንደ ሚያግዙ ይገልፃል፡፡

 

 

Tags: