በ150 ሚሊዮን ብር የተገነባው ብሔራዊ የኅብረተሰብ ጤና ማሠልጠኛ ማዕከል ተመረቀ

አሜሪካ መንግሥት የበሽታዎች ቁጥጥርና መከላከል ማዕከል (ሲዲሲ) ከአሜሪካ ፕሬዚዳንት የአስቸኳይ ዕቅድ ለኤድስ ድጋፍ (PEPFAR) ባገኘው 150 ሚሊዮን ብር ያስገነባው ዘመናዊ ብሔራዊ የኅብረተሰብ ጤና ማሠልጠኛ ማዕከል፣ መጋቢት 19 ቀን 2009 ዓ.ም. ተመርቆ ለኢትዮጵያ የኅብረተሰብ ጤና ተቋም በይፋ ተላለፈ፡፡

ማዕከሉ በብሔራዊ ደረጃ የጤና ክብካቤ ባለሙያዎችን ለማፍራት የሚደረገውን ጥረት ለማሳደግና ለማስፋት ከመርዳቱም በተጨማሪ ለብሔራዊ የኅብረተሰብ ጤና ቁጥጥር፣ ምርምርና ላቦራቶሪ ትስስር የሥልጠናና የድጋፍ ማዕከል በመሆን ያገለግላል፡፡ አዲሱ የማሠልጠኛ ማዕከል በኢፕዲሞሎጂ፣ ላቦራቶሪ ሳይንስ፣ በኅብረተሰብ ጤናና በሌሎች የሥልጠና እጥረት በሚታይባቸው ዘርፎች ሥልጠና ለመስጠት የሚያግዝ ነው፡፡

በ10 ሺሕ ካሬ ሜትር ቦታ ላይ የተገነባው ይኸው ባለ አምስት ፎቅ ሁለገብ የሥልጠና ማዕከል፣ ለጤና ጥበቃ ሚኒስቴር፣ ለዩኒቨርሲቲዎችና ለዓለም አቀፍ የጤና ድርጅቶች በምርምርና በሥልጠና የሚጠነክሩበትን መንገድ ያመቻቻል፡፡ የአገሪቱን ሕዝብ ፍላጎት የሚያሟላና ተላላፊ በሽታዎችን በመለየትና የመከላከል አቅምን በማሳደግ፤ የኢትዮጵያውያንና አሜሪካውያንን ጤና ለመጠበቅ የሚያስችል በኢትዮጵያ የሠለጠኑ የጤና ባለሙያዎችን የማዘጋጀት ጥረት አካል ነው፡፡

አዲስ የተገነባው ብሔራዊ የሥልጠና ማዕከል የአሜሪካ መንግሥት በኢትዮጵያ የኤችአይቪ ኤድስና የጤና ሥርዓት መሠረተ ልማትን ለማጠናከር የሚሠራው የረዥም ጊዜ ውጥን አካል ነው፡፡ ላለፉት 15 ዓመታት የአሜሪካ መንግሥት በሲዲሲ ኢትዮጵያ በኩል ለኢትዮጵያ የኅብረተሰብ ጤና ተቋም ለፌዴራል፣ ለክልሎችና ለላቦራቶሪዎች የአቅም ማበልፀጊያ የገንዘበና ቴክኒክ ድጋፍ ሲያደርግ ቆይቷል፡፡ በኤችአይቪ ኤድስ፣ የአባላዘርና የሳንባ በሽታዎችን የተመለከቱ የቁጥጥር ሥራዎችን ጨምሮ መርሐ ግብሮችን የመደገፍ ሥራ ያከናውናል፡፡

በኢትዮጵያ የአሜሪካ ኤምባሲ የበላይ ጉዳይ አስፈጻሚ ፒተር ቭሩማን፣ ከጤና ጥበቃ ሚኒስትር ዴኤታ ዶ/ር ከበደ ወርቁና በአሜሪካ መንግሥት የበሽታዎች ቁጥጥርና መከላከል ማዕከል የዓለም አቀፍ ጤና ማዕከል ዳይሬክተር ዶ/ር ሬቤካ ማርቲን ጋር በመሆን ማዕከሉን መርቀዋል፡፡

ሚኒስትር ዴኤታው በጤና ጥበቃ ሚኒስቴር የበላይነት የሚንቀሳቀስ የድንገተኛ ሕክምና ማዕከል ለማቋቋም የሚያስችል እንቅስቃሴ በመከናወን ላይ መሆኑን ገልጸው፣ የኢትዮጵያ የኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ከማዕከሉ ጋር በጋራና በኅብረት እንደሚሠራ አስረድተዋል፡፡