በጤና ተቋማት የእናቶች መቆያ ቤቶች አገልግሎቶችን ወጥ ለማድረግ የተዘጋጀ መመሪያ

 

መከላከልን መሰረት ያደረገው የኢትጵያ የጤና ፖሊሲ መተግበር ከጀመረበት ጊዜ አንስቶ በህብረተሰቡ ጤና ላይ እምርታዊ ለውጦች የታዩ ሲሆን በተለይም ፖሊሲውን ለማስፈፀም በተዘጋጀው የጤናው ዘርፍ የልማት መርሃ ግብር ሁለተኛ የትግበራ ዘመን ወቅት የተቀየሰው የጤና ኤክስቴንሽን ፕሮግራም ለውጤቱ ከፍተኛ ድርሻ አለው፡፡ በጤና ተቋማት ግንባታ፣በጤና ፋይናንስ ስርዓት፣በሆስፒታል ሪፎርም፣በመድኃኒት ግዥ፣ አስተዳደርና ስርጭት፣በቤተሰብ ዕቅድ አገልግሎት፣ ቅድመ ወሊድ አገልግሎት፣ በክትባት አገልግሎት እንዲሁም እንደ ወባና ኤች.አይ.ቪ/ኤድስ ያሉ ዋና ዋና ተላላፊ በሽታዎችን በመከላከልና በመቆጣጠር ረገድ የተገኙትን ውጤቶች ለአብነት መጥቀስ ይቻላል፡

ኢትዮጵያ የሕፃናትን ሞት በመቀነስ እና የምዕተ ዓመቱን ግብ በማሳካት አመርቂ ውጤት አምጥታለች፡፡ የእናቶችን ሞት በ72 ፐርሰንት የቀነሰች ቢሆንም የምዕተ ዓመቱን ግብ ከማሳካት አንፃር ከፍተኛ ክፍተት የነበረበት መሆኑ ግልፅ ነው፡፡ በዘላቂ የልማት ግቦች መሠረት በ2030 እ.አ.አ. የእናቶችን ሞት ከ70 (በ100,000 በሕይወት ከሚወለዱ ሕፃናት) በታች ማውረድ ሲሆን የጨቅላ ሕፃናት ሞት ደግሞ ወደ 12 (ከ1,000 በሕይወት ከሚወለዱ ሕፃናት) ማውረድ ነው፡፡

በእርግዝና ወቅት በወሊድና ድህረ ወሊድ ጊዜ የደም መፍሰስ ፣ከፍተኛ የደም ግፊት፤በመላ ሰውነት የተሰራጨ ኢንፌክሽን፣ እና ንፅህናውን ያልጠበቀ ጽንስ ማቋረጥ ዋናዋናዎቹ ቀጥተኛ የእናት ሞት ምክንያቶች ናቸው፡፡ ሆኖም ተገቢው ህክምና በተገቢው ሰአትና በተገቢው ቦታ በሰለጠነ የሰው ኃይል ቢሰጥ አብዛኛውን የእናቶች ሞት መከላከል እንደሚቻል በሰፊው ይታመናል፡፡ 

የእናቶች ሞት ከፍተኛ የሆነባቸው አካባቢዎች የእናቶች ጤና ክብካቤ አገልግሎቶችን ተጠቃሚ የሆኑ እናቶች ቁጥር በጣም ዝቅተኛ ነው፡፡ ለዚህም ደግሞ የእናቶች ጤና ክብካቤ አገልግሎቶች ተደራሽነት ማነስ ዋነኛ ተጠቃሽ ምክንያት  ሆኖ ይገኛል፡፡ ስለዚህም የድንገተኛ የወሊድና የጨቅላ ህጻናት ህክምናና እንክብካቤ አገልግሎትን ተደራሽነት መጨመር የእናቶችና የጨቅላ ህጻናት ሞት ለመቀነስ ዋና መሳሪያ ነው፡፡

ድንገተኛ የወሊድና የጨቅላ ህጻናት ህክምናና እንክብካቤ አገልግሎትን ተደራሽነት ለማሻሻል ሶስት አማራጮችን አሉ፡፡ እነዚህም 1. ውጤታማ የሆነ የህሙማን ቅብብሎሽ መመስረት፤ 2. ያልተማከለ የድንገተኛ የወሊድና የጨቅላ ህጻናት ህክምናና እንክብካቤ (ድንገተኛ የወሊድና የጨቅላ ህጻናት ህክምናና እንክብካቤ አገልግሎት የሚሰጡ የጤና ተቋማትን ማስፋፋት) 3. ለመውለድ የተቃረቡ እናቶችን ለጤና ተቋማት አቅራቢያ በሆነ ቦታ እንዲቆዩ ማድረግ ናቸው፡፡

ባለፉት ጥቂት አመታትም ድንገተኛ የወሊድና የጨቅላ ህጻናት ህክምናና እንክብካቤ አገልግሎት የሚሰጡ የጤና ተቋማትን በማስፋፋት እንዲሁም የህሙማን ቅብብሎሽን በማጠናከር በተለይም በርካታ ቁጥር ያላቸው አምቡላንሶችን በመግዛት እና በማከፋፈል ድንገተኛ የወሊድና የጨቅላ ህጻናት ህክምናና እንክብካቤ አገልግሎትን ተደራሽነት ለማሻሻል ከፍተኛ ጥረት ሲደረግ ቆይቷል ፡፡ ይሁን እንጂ በአንዳንድ አካባቢዎች ከመሬት መልከዓ ምድራዊ አቀማመጥ የተነሳ እነዚህ አምቡላንሶች ሁሉም አካባቢዎች መድረስ ስለማይችሉ በእነዚህ አካባቢዎች የሚገኙ ነፍሰጡር ሴቶች የመውለጃ ጊዜያቸው ሲደርስ የሚቆዩበትና የባለሙያ የቅርብ ክትትል የሚያገኙበት  እነዲሁም ከወለዱ በኃላ ከ24-48 ሰዓት ከጨቅላ ሕጻናቱ ጋር የሚቆዩበት ስፍራ ማዘጋጀት አስፈልጓል፡፡ አተገባበሩም በሁሉም አካባቢዎች ወጥ ይሆን ዘንድ ይህ መመሪያ ተዘጋጅቷል፡፡