ሕይወት እየሰጠች እናት ለምን ትሙት?

 

ሕይወት እየሰጠች እናት ለምን ትሙት፣ ክፉ ቀን ይለፋት ሞት እራሱ ይሙት፣

ሚድዋይቭ ቀን አመታዊ በአል ሲከበር ከተዘመረው መዝሙር የተወሰደ ስንኝ ነው ከላይ ያነበባችሁት።  የአለምአቀፉን ሚድዋይቭ ቀን ምክንያት በማድረግ አንዳንድ ቁምነገሮችን ለአንባቢ ማለታችን ይታወሳል። ከዚያው ሳንርቅ እናቶችን በማዋለድ እና ጨቅላ ሕጻናቱን በመጀመሪያ በመቀበል ደረጃ የተሰማሩ ሚድዋይቭችን አቅምና ክህሎት በማዳበር በኩል እንዲሁም በስራ ስምሪታቸው የሚያጋጥሙ ምን ነገሮች አሉ? ከሚል በበአሉ ላይ ቀርበው ከነበሩ ጥናታዊ ስራዎችና የተግባር ምስክሮች የመረጥነውን ለዚህ እትም ብለናል።

ጥያቄዎችም መልስ የሰጡን ሲ/ር አስቴር በርሔ እና ሲስተር ምንትዋብ ገላጋይ ነቸው።

ጥያቄ፡ ሚድዋይቭ  ትርጉሙ ምን ማለት ነው?

ሲ. አስቴር፡ ሚድዋይቭ ማለት ከእናት ጋር መሆን የሚል ትርጉም ነው ያለው። በኢትዮጵያ የእነዚህ በሚድዋይቭ የሚሰለጥኑ ባለሙያዎች ትምህርት መሰጠት የተጀመረው በ1953 ዓ.ም ነው። የተጀመረውም በፌስቱላ ሐኪም ቤት መስራቾች በነዶ/ር ሐምሊን ነው። እነዚህ ባለሙያዎች ወደ አትዮጵያ የመጡትም የሚድዋይፍ ትምህርት ቤትን ለመክፈት ሲሆን በመጀመሪያው ስራቸውም አራት ሴቶች ነበሩ የተመረቁት። ቀደም ባለው ጊዜ ግን አንድ አስተሳሰብ ነበር - ይኼውም ሙያውን የሴት ሙያ አድርጎ የመውሰድ። ግን ዛሬ ግን ሙያው የሁለቱም ማለትም የሴትም የወንድም ሙያ መሆኑን ተግባር ምስክር ሆኖ እያሳየን ይገኛል።

ጥያቄ፡ ወንድ ሚድዋይፍ በምደባ ወይስ በፍላጎት ነው ትምህርቱን የሚማሩት?

ሲ. አስቴር፡ እኔ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በአስተማሪነት ወደ 11 አመት ሰርቻለሁ። በዚህ ጊዜ ያየሁት ነገር ወደትምህርቱ ሲመደቡ ፍላጎት ያላቸው ሲኖሩ ምናልባት በምደባ ሳይፈልጉ የገቡበትም ቢሆን እንኩዋን ከገቡ በሁዋላ ተግባሩን ወድደው እንዲያውም በከፍተኛ ውጤት ሁሉ የሚመረቁ እንዳሉ ተገንዝቤአለሁ። ትምህርቱ ይሰጥ የነበረው በመጀመሪያ በዲፕሎማ ደረጃ ሲሆን በሁዋላ ግን ወደ ዲግሪ ተቀይሮአል። ቀደም ሲል በዲፕሎማ የተመረቁትም ቢሆኑ በወጣው መስፈርት መሰረት ደረጃቸውን አሻሽለው እና ተወዳ ድረው እየገቡ ዲፕሎማቸውን ወደዲግሪ የመቀየር እድል አግኝተዋል። በእርግጥ ቀደም ሲል ሙያው ከነርስነት ሙያ ጋር የተደባለቀ ሲሆን ነገር ግን በአለም አቀፍ ደረጃ ሙያው እራሱን የቻለ ሙያ ነው ከሚል ስምምነት በመደረሱ ራሱን ችሎ እንዲወጣ ተደርጎአል።

ጥያቄ፡ የእናቶች ምርጫ ወደማን ያደላል? ሴት ወይንስ ወንድ ሚድዋይፍ ?

ሲ. አስቴር፡ በአገራችን ሚድዋይቭ ትምህርት ላይ የወንዶች ቁጥር እየጨመረ ሲሔድ ሁኔታ ውን መለስ ብሎ ማስተዋል በማስፈለጉ የኢፊድሪ ጤና ጥበቃ ሚኒስር በህብረተሰቡ ዘንድ ተቀባይነት እያገኘ ነው ወይንስ አይደለም የሚለውን ማስጠናት ፈለገ። መረጃውን መሰብሰብ ያስፈለገውም በቀጣይ ለሚሰሩ ስራዎች እቅድና ንድፍ ለማመቻቸት እንዲረዳ ታስቦ ነው። በዚህም መሰረት እንደተገኘው የዳሰጥናት ስራ ውጤት ከሆነ ከተጠቃ ሚዎቹ ሴቶች ከግማሽ በላይ በሴቶች አገልግሎቱን ማግኘቱን እንደሚመርጡ ታውቆአል። በእርግጥ ይህ ውጤት በመላው ኢትዮጵያ ተመሳሳይ ነው ለማለትም አያስደፍርም። ምክንያቱም አንዳንድ የናሙና ጥናቶች  እንደሚያሳዩት  ከቦታ  ቦታ  ልዩነት  ስላለው ነው። በተለይም በገጠሩ አካባቢ እንዲሁም የሙስሊም እምነት ተከታዮች እንዲሁም አርብቶ አደር አካባቢ ያሉት እናቶች እንደተናገሩት ከሆነ ሴት ሚድዋይፍን ይመርጣሉ። ስለሆነም አንዳንድ ቦታዎች በተደረገው ጥናት በወንዶች ሚድዋይፍ መጠቀም አንፈልግም ባሉባቸው አካባቢዎች አንዳንድ የመፍትሔ እርምጃዎች መወሰዳቸውንም አይተናል። ለምሳሌም ...ወንድ ሚድዋይፍ በተመደቡበት ገጠራማ ቦታ የወላዶች ቁጥር ሲቀንስ ወንዱን ወደከተማ በመመደብ ሴቶቹን ወደገጠሩ ገብተው እናቶችን እንዲያዋልዱ የተደረገበት ሁኔታ ታይቶአል። ይህ በመደረጉም እናቶች የስነተዋልዶ ጤና አገልግሎቱን ወደሕክምና ተቋም መጥተው እንዲጠቀሙ የበለጠ እድሉን ለማስፋት አግዞአል። ከዚህ በተጨማሪም በምሽት እንዲሁም ቅዳሜና እሁድ እና በበአላት ቀን ወንድ አዋላጅ ነርሶችን ብቻ ከመመደብ ሴትና ወንድ እያቀላቀሉ በመመደብ ችግሩን ማቅለል ተችሎቸል።

ጥያቄ፡ ይህ ችግር ጎልቶ የሚታይባቸው አካባቢዎች የትኞቹ ናቸው?

ሲ. አስቴር፡ አሁን ለምሳሌ ሱማሌ ክልል፣ ወደ ኦሮሚያ፣ አፋር አካባቢ በተለይም የሙስሊም እምነት ተከታዮች የሆኑ በጥናቱ ለናሙና የተካተቱ እናቶች ካልተቸገሩ በስተቀር የወንድ ሚድዋይፍ እንዲያያቸው እንደማይፈልጉ ነው። በጥያቄው ከተነሱት መካከል.. በጤና ተቋሙ ካለወንድ በስተቀር ሴት ሚድዋይፍ ባይኖሩ  አገልግሎቱን  አንፈልግም  ትላላችሁ?  ሲባሉ...በጣም ችግር ከሆነማ ምን አማራጭ አለን? የሚል ነበር መልሳቸው። ያ ማለት ግን በውዴታ ነው የተጠቀሙት ማለት አይቻልም። ስለዚህ ስለነዚህ ማህበረሰብ ክፍሎች ማሰብና መጨነቅ እንዲሁም የአሰራር ዘዴ መንደፍ ያስፈልጋል።  ትምህርቱን  በአንድ  በኩል  በማስተማር ነገር ግን ባህላቸውንም ማክበር ስለሚያስፈልግ ሴቶችን መመደብ ግድ ይሆናል።

ጥያቄ፡ ትምህርቱን በማስተማር ሊሻሻል የሚችል ነገር ይኖራል?

ሲ.   አስቴር።   ይኖራል።   ምክንያቱም   ለምሳሌ የጽንስና ማህጸን ሐኪሞች በአብዛኛው ወንዶች ናቸው። ስለዚህ ማንኛዋም ታካሚ በወንድ ዶክተር ለመታየት ችግር አይታይባትም። አዋላጅ ነትም ልክ እንደማህጸን ሐኪሙ የህክምና ሙያ ስለሆነ ለመጠቀም እንዳይሳቀቁ ማስተማር አለብን። ስለዚህ ወንድም ሆነ ሴት ዋናው ተግባራቸው እናትየውን ልጅ ማዋለድ ስለሆነ ይህንን ከግንዛቤ እንዲያስገቡ ጥንካሬ ያለው ትምህርት መስጠት ያስፈልጋል። እውጤት ላይ እስኪደረስ ግን የእናቶቹን መብት ለማክበር አስፈላጊውን ጥረት ማድረግ ተገቢ ይሆናል። የእናትየውን የስነ ተዋልዶ ጤና መብት ማክበርና የማህበረሰቡንም የግንዛቤ ደረጃ መረዳት ያስፈልጋል። ዋናው አላማ እናቶች በሰለጠነ ሰው በጤና ተቋም እንዲወልዱ ሁኔታዎችን ማመቻቸት ነው።

ሲ/ር ምንትዋብ ገላጋይ ሚድዋይፍን ክህሎትና ብቃት በማጠናከር በኩል ምን እየተሰራ ነው? ለሚለው ጥያቄ ማብራሪያቸውን ሰጥተውናል። ሲ/ር ምንትዋብ ጄፓይጎ ከሚባል ድርጅት የተወከሉ ሲሆን ለጤናው አገልግሎት የሰው ኃይሉን አቅም ማጎልበትን በሚመለከት ከጤናጥበቃ ሚኒስርና ከዩኤስአይዲ ባደረገው የጋራ ስምምነት  በ4  መስተዳድሮች  ላይ  የሚሰራ  መሆኑን ነው የገለጹት። የፕሮጀክቱ ትኩረትም የትምህርት አቅምን ከማጎልት በተጨማሪም የሚድዋይፍ ቁጥር መጨመርን የሚመለከት ነው። “አንዱና ዋነኛው ስራው ሚድዋይፍ በተለይም ከትምህርት ቤት ተመርቀው የሚወጡት የተሻለ ጥራት ያላቸው እንዲሆኑና ሙያቸውንና ግዴታቸውን በሚገባ ተረድተው እና አውቀው ግዴታቸውን እንዲወጡ ማስቻል ነው። ይህ ፕሮጀክት የተጀመረው በፈረንጆች አቆጣጠር 2012 ሲሆን በመጀመሪያ የተደረገው በመስራት ላይ ያሉት ሚድዋይፎች ስንት ናቸው? ?ቁጥራቸው ይበቃል ወይ? ይጨመር ቢባልስ በምን ያህል ነው መጨመር ያለበት ? ሌላ መሟላት ያለበት ጎደሎ ነገርስ ምንድነው የሚለውን ጥናት ተደርጎ ይህንን ለማሟላት ምን ቢደረግ ይሻላል? ወደሚለው ምክክር ነበር ከጤና ጥበቃ እና ከሌሎች አጋር ድርጅቶች ጋር የተዘለቀው። ወደከፍተኛ ተቋም ትምህርት ምደባው ሁኔታ ስንዘልቅ ብዙው የትምህርት ክፍል ተመድቦ ካበቃ በሁዋላ በስተመጨረሻ የሚመደቡ በመሆኑ በተለይም ወንዶቹ ሌላ የተሻለ ትምህርት አለ ብለው ያስባሉ። እናም ተማሪዎች ብዙውን ጊዜ ያንን ትምህርት መርጠውት አይመጡም ነበር።

ስለዚህም ስለሙያው የግንዛቤ ማዳበሪያ ስራዎች በመገናኛ ብዙሀን በትምህርት ቤቶች መስራት ያስፈልግ ስለነበር ተሰርቶአል። ከዚያም በሁዋላ ሚድዋይፍ ትምህርት ልክ እንደሌሎች ትምህርቶች ተማሪዎች መርጠውት በእኩል በምደባ የሚገቡበት ሆነ። በዚህም ሂደት የትምህርት መርጃ መሳሪያዎችን ከተለያዩ እገዛ ከሚያደርጉ ድርጅቶች ጋር በመተባበር ገዝቶ መስጠት አንዱ የስራ ጎን ነበር። ከዚህም በተጨማሪ ተማሪዎች ልክ ከትምህርት ቤት በከፍተኛ ውጤት እንደተመረቁ ምንም የስራ ልምድ ሳይኖራቸው ወደ አስተማሪነት የሚመደቡ ስለሆነ እነዚህ ሰዎች ስልጠና እንደሚያስፈልጋቸው እሙን ነው።

እውቀታቸውን ማጎልበት ያስፈልጋል በሚል መምህራን የማስተማሪያ ዘዴ ትምህርቶችን፣ የማዋለድን ችሎታ ማጎልበትን የሚመለከቱ ስልጠናዎች የተሰጣቸው ሲሆን በአፈጻጸም በኩል ያለውንም ለመመልከት ተሞክሮአል። በስተመጨረሻም ይህ ፕሮጀክት ሲያልቅ ስራው ቀጣይነት እንዲኖረው መንግስት የሚረከብበትን ሁኔታ በማመቻቸት በቀጣይነት ድጋፍ ሰጪዎች ቢኖሩም ባይኖሩም ትምህርት ቤቶች የወጣውን የአሰራር መመሪያ ተከትለው እንዲቀጥሉ መስመር ተዘርግቶአል። ” ብለዋል ሲ/ር ምንትዋብ ገላጋይ።

Source-Addis Admas Newspaper

 

Tags: